የሐሙስ ውዳሴ ማርያም
የሐሙስ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ #ሐሙስ ለምስጋና አራተኛ ለፍጥረት አምስተኛ ቀን ነው፡፡ በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ዙፋን ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኹናም ሊቁን ባርካው ምስጋናዉን ጀምሯል፡፡ ከወትሮ ይልቅም ነቢያትንና ሐዋርያትን አስከትላ መጥታለች፡፡ ፩. ነደ እሳት ሰፍሮባት፣ በነደ እሳት ተከባ፣ ጫፎቿ ሳይቃጠሉ ሙሴ በደብረ ሲና ያያት ዕፅ ድንግል ማርያምን ትመስላለች /ዘጸ.፫፡፩-፫/፡፡ አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኹኗልና፤ ባሕርየ (እሳተ) መለኮቱም አልለወጣትምና (አላቃጠላትምና) ሐመልማላዊቱ ዕፅ እመቤታችንን ትመስላለች፡፡ ዳግመኛም እርሱን ከወለደችው በኋላ ማኀተመ ድንግልናዋ አልተለወጠምና ሐመልማላዊቱ ዕፅ እመቤታችንን ትመስላለች፡፡ እርሱም ምንም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ ፍጹም ሰው ቢኾንም ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠምና እሳቱን ይመስላል፡፡ ሰውም ቢኾን ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠምና ሰው ኾኖ ያዳነን የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ሰው ኾኖ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋዉን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡ ፪. ይቅርታሽ (ምልጃሽ) ለኹላችን ይኾን ዘንድ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ! ኹላችን እናከብርሻለን፤ እናገንሻለን፡፡ ሔዋን ባደረገችው ዐመፅ በባሕርያችን ጸንቶ የነበረ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ በእርሷ ምክንያት የጠፋልን አምላክን የወለደች ድንግል ማርያም የኹላችን መመኪያ ናት፡፡ “ሔዋን ምን አደረገች?” ትለኝ እንደኾነም ዕፀ በለስን በልታለች እልሃለሁ፡፡ “ወአዘዞሙ ለኪሩቤል ወሱራፌል ዘውስተ እደዊሆሙ ሰይፈ እሳት እንተ ትትመያየጥ ከመ ይዕቀቡ ፍኖተ ዕፀ ሕይወት - ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩ...